Friday, March 30, 2012

የለገዳዲ የቅድስት ኪዳነ ምህረት ፅላት ተአምር

     /በደረጀ ነጋሽ ዘወይንዬ/
        ዓርብ የካቲት 16/2004 ዓ.ም በጠዋቱኑ እጅግ በርካታ ምዕመናን በቅርብ በተገኘው የለገዳዲ ኬማ ዋሻ ፍልፍል ቤተክርስቲያን በአግራሞትና አድናቆት ተሰብስበዋል፡፡ በአካባቢው ድንኳኖች ተጥለዋል፡፡ አንዳንዶች ዋሻ ሲጎበኙ ሌሎች ደግሞ ፀበል ይጠመቃሉ፡፡ አንዳንዶች ይፀልያሉ ሌሎች ደግሞ ይነጋገራሉ፡፡ የከተማው ወይዛዝርት ለመስተንግዶው ይፋጠናሉ፡፡ እሺ ብላ ከዋሻው ትወጣ ይሆን? ወደ ዋሻው ካልተመለሰችስ? ብቻ የየራሳቸውን አስተያየት ይሰጣሉ፡፡ ለገዳዲ ከተማ ከአዲስ አበባ 25ኪ.ሜ ርቀት ላይ በኮተቤ መስመር ለገጣፎን አልፈው የምትገኝ ከተማ ስትሆን በወታደር ማሰልጠን፣ በትምህርት ስርጭት እና በውሃ አቅርቦት ትታወቃለች፡፡ ለገዳዲ ማለት በኦሮምኛ የጠጅ ወንዝ ማለት ነው፡፡ በዚህ ቦታ ገበሬዎች የፈረሰ ቤተክርስቲያን፤ ፀበል ይገኛል፣የአባቶቻችን መካነ መቃብር እዚህ ነው እያሉ በጉልበት ያለፍቃዳቸው አስፈራርተዋቸው ቦታውን ለኤንጂኦ ተሰጠ፤ አራት ዓመት ምንም ሳይሰራበት ቆየ፡፡ በብዙ ተንኮል ያገኘውን የቤተክርስቲያን የሃይማኖት ቦታ ሊሠራበት አጥር ማጠር ሲጀመር ዋሻ እንዳለ ለአባቶቻችን በህልም ታያቸው፡፡ ወደ ቦታው ሲሄዱ ከስር ከወንዝ አደገኛ ገደል ላይ ትንሽ ቀዳዳ ዐዩ፡፡ አፈር ሲቆፍሩ ፍልፍል ዋሻውን አገኙ፤ ዋሻው በሶስት ይከፈላል፡፡ የመጀመሪያው ቤተ መዛግብት፣ ቤተልሔም(አፅንኦባእት)፣ የተጋድሎ ቦታ አፅመቅዱሳን የተለያዩ መገልገያዎች እና ቅርሶች ይገኛሉ፡፡
   
እንዲሁም ወደ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ፀበል የሚወስድ የውስጥ መንገድ በእግር ግማሽ ያህል እንደሄዱ ተዘግቷል፡፡ ወደ ሁለተኛው ዋሻ ሲገቡ ደርብ በግራ በኩል መሰወሪያ በቀኝ ሲወርዱ ቅኔ ማኅሌት ቅድስት መቅደስ ይገኛል፡፡ ከዚያ ወጥተው ወደ ሦስተኛው ዋሻ ሲገቡ ወደ ውስጥ እንደገቡ አንገት ብቻ ወደ ላይ በሚያስወጣው ሲመለከቱ በግራ በኩል በድንጋይ የተዘጋ እስካሁንም ያልተከፈተ በቀኝ የቅደስት ኪዳነ ምህረትን ፅላት ያለበትን ዋሻ ያያሉ፡፡ በርካታ ፅላትና ቅርሶች እንደሉና ከፅላቶቹም ውስጥ የቅድስት ስላሴ እና የቅዱስ ገብርኤል እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ግን የት ቦታ እንደሆነ እስካሁን ማወቅ አልተቻለም፡፡ ተጨማሪ በርካታ በተለያየ ቦታ ዋሻዎች ይታያሉ፡፡ እንዲ አይነት ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ግኝታቸው ከጠላት ሽሽት በዮዲት ጉዲት ከ842 እስከ 882 ዓ.ም ወይም ግራኝ መሐመድ ወረራ 1515 እስከ 1530 ዓ.ም እንደሆነ ይገመታል፡፡ ለወረዳው ምክርቤት ቀድሞ የዋሻ ፍልፍል ቤተክርስቲያን ከዛም ህዳር 16/2004 ዓ.ም የእናታችንን የቅድስት ኪዳነ ምህረት ፅላት እንደተገኘ ተነገረ፡፡ ኦርቶዶክሳዊያኑ ደስታው ገደብ አጣ ወረዳው እና ኤንጂኦው ግን ይህ ነገር አልተዋጠላቸውም፡፡ ሕዝቡ ይህ ቀድሞም የሃይማኖት ቦታ ነበር፤ በግድ ለኤንጂኦ ተሰጠ፤ አሁን ደግሞ ዋሻ ቤተክርስቲያን ፅላት አፅመ ቅዱሳን ታሪካዊ ቅርሶች ተገኝተዋል እና ኤንጂኦው ሌላ ምትክ መሬት ይውሰድ ካልሆነም ለገበሬው የከፈለው ብር 347,000.00(ሶስት መቶ አርባ ሰባት ሺ ብር) ይመለስለት አሉ፡፡ ይህ ግን አዎንታዊ ምላሽ አላገኘም ከወረዳው እና በምዕመናን መካከል ያለው አለመግባባት ቀጠለ፡፡ ለመሆኑ ኤንጂኦው የማነው? ከውጭ የሚረዳው በነማን ነው? ኤንጂኦው በነፃ መሬት እንዲወስድ መንግስት ይፈቅዳል፡፡ እሱ ግን ለምን ብር ከፈለ? ለምን የሃይማኖት ቦታ ተመረጠ? አንድ ሰው መሬት ወስዶ አራት ዓመት ሙሉ አለመስራቱ መሬቱን አያስነጥቀውም ወይ? ከዚህ በፊት ጣሊያኖች በዚህ የሃይማኖት ቦታ ካምፕ መስርተው ብዙ ጥናት አደረጉ፡፡ ግን አልተሳካላቸውም፡፡
     ኤንጂኦው ሌላ ቦታም ሆነ ገንዘብ አልፈልግም ማለቱ አመጣጡ ለሰባዊነት ነው ወይስ ታሪክን ማጥፋትና ቅርስ ፍለጋ ነው? በአካባቢው ንዋያተ ቅዱሳኑና ታሪካዊ ቅርሶች እንዳሉ ቀድሞም ይነገራል፡፡ በጣሊያን ጊዜ ባንዳ ነበር አሁንም ባንዳ አለ፡፡ ‹‹የዘሬን ብለቅ… ››አይደል የተባለው፡፡ የአህያ ቆዳ የለበሰ ጅብ ጅብ እንጂ አህያ ሊሆን አይችልም፡፡ የለገዳዲ እና የአካባቢው ሕዝብ፣ ካህናቱ፣ በርካታ የአዲስ አበባ ምዕመን አንድ ልብ ሆነው እየፀለዩ ይገኛሉ፡፡ ካህናቱ የቅድስት ኪዳነምህረትን ፅላት በዋሻው ውስጥ እየተቀያየሩ ፀሐይና ብርድ እየተፈራረቀባቸው ሌሊትና ቀን ይጠብቃሉ፡፡ የካቲት 16/2004 ዓ.ም ደረሰ፡፡ የቃል ኪዳኗ ታቦት በቃል ኪዳን ቀን ለማክበር ካህናት ወደ ዋሻው ገብተው ታቦቷን ተሸክመው ወደ ዋሻው ድንኳን መጡ፤ እልልታው ቀለጠ ግማሹ በደስታ ያለቅሳል፤ ዝማሬ ምድርን ከደነ ቀድሞ የፈረሰው አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን ጋር የተጣለው ድንኳን ደረሱ፤ ታቦቱ ተሸካሚው ካህን ምልክት አሳዩ፤ ታቦቱን መሸከም አልቻልኩም አቃጠለኝ ካህን ይቀየርልኝ አሉ፡፡ በሌላ ካህን ተቀየሩ ሕዝቡም እንዲረጋጋ ተነገረው፡፡ ወረብ ስብከት ወደፊት ለሚሰራው መቃኞ ቤተክርስቲያን ብር ተሰበሰበ፤ ስርዓተ ቅዳሴ በድንኳኑ ውስጥ ተከናወነ፡፡ ከዚያም ታቦተ ቅድስት ኪዳነ ምህረትን ይዘው ከድንኳን ጉዞ ተጀመረ፡፡ ለወንጌል ማስፋፋት ዘወትር የሚደክሙት ደከመኝ ሰለቸኝ የማይሉት የለገዳዲ ወጣቶች ቀይ ቲሸርት ለብለው ቀይ ምንጣፍ የሚያነጥፉ ታቦቷን ወደ መጣችበት ዋሻ ለመመለስ ይዘምራሉ፡፡ ድንገት ድምፅ ተሰማ አልቅሱ ምዕመናን፣፤ አልቅሱ እግዚአብሔር እንዲታረቀን አልቅሱ የሚል በሞንታርቦ ድምፅ ተሰማ፡፡ ምዕመናን ሁሉ ተደናገጡ፤ ታቦተ ኪዳነ ምህረትን የተሸከሙትን ሁለተኛው ካህን ታቦቷ ጥላቸው ከአናታቸው አልወርድም አለች፡፡ የወደቁት ካህን እያለቀሱ ድምፅ አሰሙ፡፡ ተቃጠልኩ አንሱልኝ አልቻልኩም እግዚኦ በሉ ብለው በወደቁበት ይጮኃሉ፤ ግን ማን ታቦቷን ያንሳላቸው፡፡ እሳትን ማን ይደፍራል፡፡ ጩኸቱ፣ ምህላው፣ ለቅሶው፣ እግዚኦታው ቀጠለ፤ ግን ማንም ታቦቷን ማንሳት አልቻለም፡፡ ሕዝበ ክርስቲያን እንደ ሻሽ ተነጥፈው አለቀሱ፡፡ መነኮሳት እና ካህናት አነቡ፤ በብዙ ለቅሶና እግዚኦታ ታቦቷን አንስተው ለሶስተኛ ሰው ቆሞስ ለሆኑት መነኩሴ ተሰጠ፡፡ እሳቸውም ወደ ዋሻው ለመውሰድ እራመዳለሁ ሲሉ ጣለቻቸው፡፡ አሁንም ለቅሶ አሁንም እግዚኦታ ቆሞሱ አባታችን በወደቁበት ቦታ ሆነው ወደ ዋሻ መመለስ እንዳልፈቀደች ወደ ዋሻ አትመልሱኝ ክብሬ መገለጫው ደርሷል፤ ወደ ድንኳን አስገቡኝ ብላለች ሲሉ በቀላሉ ብድግ አለችና ወደ ድንኳን ገባች፡፡ ሁለተኛው ታቦት ተሸካሚው ካህን ከወደቁበት ለማንሳት ተሞከረ፤ እራሳቸውን ስተው በሕይወትና በሞት መካከል ሳሉ ወጣቶች ካህኑን ከካህን ጋር ይዘው ወደ ፀበል ሮጡ፤ ታቦት ተሸካሚው ካህን ሲጠመቁ በእሳት የጋለ ብረት ምጣድ ውሃ ሲፈስበት የሚያወጣውን ድምፅ እና ጭስ እሳቸው ላይ ታየ፤ ከብዙ ሰዓታት ቆይታ በኃላ እራሳቸውን አወቁ፡፡ ካህናቱ የወደቁት ኃጢያተኛ ስለሆኑ ሳይሆን የቅድስት ኪዳነ ምህረት ፅላት ወደ ዋሻ አልገባም ብላ በተአምራቷ ቦታውን ስለአስከበረች ነው፡፡ የወረዳው ምክር ቤት ፍልፍል ቤተክርስቲያን ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ቦታነቱን የታቦቷን ሃያልነት አምነው ተቀበሉ፡፡ ግን ቦታውን እስካሁን ለቤተክርስቲያኗ አልሰጡም ለምን? ጠንካራ የለገዳዲ ምዕመናን በሁለት ቀን ውስጥ መቃኞ ቤተክርስቲያን ሰራ:: ማታ ማታ ምህላ ይደርሳል፡፡ ሕዝበ ክርስቲያን ከተለያየ ቦታ እየመጡ እየተፈወሱ ናቸው፡፡ ሁሉም ድንኳኗን ከበው አዳራቸው እዛው ሆኗል፡፡ እግዚአብሔርም ፈቅዶ እሁድ መጋቢት 16/2004 ዓ.ም ፅላቷን ከድንኳን ወደ መቃኞ ልትገባ ችላለች፡፡ መርሃ ግብሩም እጅግ ደስ የሚል እና ብዙ ምዕመናን የተገኙበት ነበር፡፡ እርሶም ቦታው ድረስ ሄደው ከበረከቱ ተካፋይ ይሆኑ ዘንድ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር


1 comment:

  1. Sands Casino | Play online or in-person at the Sands Hotel
    Play the worrione latest 바카라 and greatest slots and table games at Sands Casino - the finest casino experience in 샌즈카지노 Las Vegas! Featuring more than 2600 electronic games and

    ReplyDelete

ማህበረ ቅዱስ አሞኒ