(ማህበረ ቅዱስ አሞኒ መጋቢት 17/2004) ለገዳዲ ዋሻ ኪዳነ ምህረት በኮተቤ መስመር ከአዲስ አበባ 25 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከለገጣፎ ከተማ አለፍ ብላ የምትገኝ ስትሆን እናት አባቶቻችን በሐይማኖት ጠብቀው ጽላተ ሙሴን ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያን ለመጠበቅ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያን ፈልፍለው ለእኛ ለልጆቻቸው ካቆዩልን የበረከት ስፍራ አንዱ ነው፡፡ በዚህ የበረከት ስፍራ የፈረሰና ቅርፁ ያልጠፋ ቤተ መቅደስ፣
በርካታ የተከፈቱ ዋሻዎች፣(የእመቤታችን የቅድስት ኪዳነ ምህረት ጽላት፣ ንዋተ ቅድሳትና የግብር ቤት ዕቃዎች የተገኙበት)፣ ያልተከፈቱ ዋሻዎች፣ መቼ እንደፈለቀ የማይታወቅ ፈዋሽ ፀበል፤ ጽላቷ ከተገኘች እና በድንኳን ካረፈችበት ጊዜ ጀምሮ የፈለቁ ፀበሎች፤ አፅመ ቅዱሳንና ንዋየ ቅድሳት የተገኙበት ሥፍራ ነው፡፡ ትላንት መጋቢት 16 ቀን 2004ዓ.ም የለገዳዲ ቅድስት ኪዳነ ምህረት ፅላት ወደ ተሰራላት መቃኞ ስትገባ የቤተክርስቲያን አባቶች፣ ሰባኪያን፣ ዘማሪያን፣ መንፈሳዊ ማህበራት፣ አርቲስቶች፣ ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ምዕመናን እና የእናታችንን ታምሯን በመስማትና በማየት ከእስልምና የመጡ ወንድሞች በቦታው ተገኝተው በዓሉን ያደመቁ ሲሆን በዕለቱም እናታችን በመቃኞ መቆየት የለባትም በማለት ያማረ ቤተክርስቲያን ለመስራት አስገራሚ የሆነ የገንዘብ ማሰባስብ ስራም ተሰርቷል፡፡
በዚህም የገንዘብ ማሰባሰቢያ የተለያዩ ምዕመናን ከፍተኛ ርብርብ ያደረጉ ሲሆን ህንፃ ቤተክርስቲያኑ ይፈጃል የተባለውን ወጪ እና ማቴሪያል ለማሰባሰብ በተደረገው ቅስቀሳም ከአውደ ምህረቱ በተላለፈው መረጃ መሰረት፡-
- 125,000.00 ብር በዕለቱ በእጅ የገባ (የውጭ ገንዘብ ምንዛሬዎችና ቼኮች ሳይጨምር)
- 307,550.00 ብር በቃል የተገባ
- 461 የጣራ ቆርቆሮ ቃል የተገባ
- 605 ኩንታል ሲሚንቶ ቃል የተገባ እና በስተመጨረሻም በቦታው ያልተገኙ አንድ ምዕመን የጎደለውን በሙሉ ለመሙላት ዝግጁ ነኝ በማለት ቃላቸውን በስልክ ሊሰጡ መቻላቸውን ለማወቅ ችለናል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ምዕመናን በስፍራው ተሰብስበው ድንቅ የእግዚአብሔርን ስራ እያዩ በመፈወስና በበረከት እየተጎበኙ ያሉ ሲሆን እርስዎም በዚህ ሥፍራ ተገኝተው ከእመቤታችን በረከት ከቅዱሳን ጸሎት ይሳተፉ፡፡
No comments:
Post a Comment
ማህበረ ቅዱስ አሞኒ