/በመምህር ነቅዓጥበብ ከፍያለው/
ይህንን ቃል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሮታል፡፡ ለጊዜው በእግር ለሚከተሉት በኃላ ግን በሥራ ለሚመስሉት፤ ቃሉን ለሚጠብቁት፤ መስቀሉን ተሸክመው በሞት ለሚዛመዱት ለሐዋሪያት ይህንን ቃል ነግሮአቸዋል፡፡ ጌታችን መዳኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ሲያስተምር መፅሐፍትንና ጥቅሶቻቸውን ብቻ አይደለም፡፡ ነገር ግን በስራ እየገለጠ ምግባርንም ያስተምራቸውም ነበር እንጂ፡፡ ጌታ እርሱ ያላደረገው(ያልሰራው) እኛን ብቻ ስሩ ያለው ምንም ነገር የለም፡፡ ስለዚህ መድሃኒታችን ‹‹ከእኔ ተማሩ›› በማለት በስራ የሚያሳየውን በጎ ስራውንም እንድንማር እየጋበዘ ነው፡፡ ከእርሱ የምንማረው ምንድነው? ብለን ስንጠይቅ
ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር የመጣው ስለሁለት
ነገር ነው፡፡ የመጀመሪያው ቤዛ ለመሆን ሲሆን ሁለተኛው አርአያ ለመሆን ነው፡፡ አርአያ መሆን ማለት ምሳሌ ፣ አብነት፣ መምህር
መሆን ማለት ነው፡፡ ጌታ ከኔ ተማሩ ማለቱ ይህንንም አርአያዬን ተመልከቱ ማለት ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ቃል ሁለት ዋና ዋና ነገሮች
ሊያስተምረን ይወዳል የዋህነትንና ትህትናን፡፡ የዋህነት ማለት ነገሮችን ሁሉ በበጎ መተርጎም ማለት ነው፡፡ መጥፎ እንኳን ቢሆን
በጎ ገፅታ መስጠት ማለት ነው፡፡ የዋህ በጥፊ ሊመቱት ሲሉ ሊያጎርሱኝ ነው ብሎ አፉን ይከፍታል ይባላል በአባቶቻችን ቢሒል፡፡ ጌታችን
መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዘንግ በመቱት ፣ ለተፉበት፣ ለተዘባበቱበት፣ የእሾህ አክሊል ለደፉበት በመስቀል ለቸነከሩበት ሰዎች
‹‹አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁም እና ይቅር በላቸው›› በማለት ስለክፉ ፈንታ በጎ ምላሽን በመስጠት የዋህነቱን አስተምሯል፡፡
ሉቃ 23፤34 ይህንንም ብዙ ሊቃውንት ‹‹ በግዕ›› እያሉ ይገልጡታል፡፡ በግ በተፈጥሮ የዋህ ስለሆነ ለጌታም የበግን ገፀ-ባህሪ
አላብሰው ይናገራሉ፡፡ አባ እርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ‹‹በሚሸልተው ሰው ፊት አፉን ከፍቶ የማይጮህ በግ እንደምን ያለ ነው?››
እያለ በአድናቆት ይጠይቃል;; የጌታችን የየዋህነት ስራ ቢነገር አያልቅም፡፡ ይህ ሁሉ ግን እኛ እንድንማርበት የተደረገ ነው፡፡
ይህንንም ቅዱስ ጴጥሮስ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንደትከተሉ ምሳሌ
ትቶላችሁ ስለእናንተ መከራን ተቀብሏልና፡፡ እርሱም አጢያት አላደረገም ፤ ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም ፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም
መከራም ሲቀበል አልዛተም፤ ነገር ግን በፅድቅ ለሚፈርደው እራሱን አሳልፎ ሰጠ፡፡ በማለት የትዕግስቱንና የየዋህነቱን ብዛት ገልጧል፡፡
1ኛ ጴጥ 2፤21-23 ይህንን ነው ጌታ ከኔ ተማሩ የሚለው፡፡ ሰዎች ቢበድሉን ይቅርታ ማድርግ እንዲገባን እና ስለክፉ ፈንታ መልካምን
እንድንመልስ እንጂ በቀል እንደማይገባ ያስተምረናል የዋህነት ጅል መሆን፣ አላዋቂ መሆን ማለት አይደለም፡፡ አዋቂ ሆኖ ተንኮልን
ሁሉ ለበጎ ነው ብሎ ለፈጣሪ መስጠት ማለት ነው፡፡ የዋህነት ከማንም ሰው ቢሆን ውለታ አለመፈለግ ነው፡፡ ለእዚነህ ሰዎች እግዚአብሔር
ቅርብ ነው፡፡ መዝ 33፤18 እነዚህ ሰዎች መንግስተ ሰማያትን እንደሚረከቡ እርሱ ባለቤቱ ተናግሯል፡፡ ማቴ 5፤5 ስለዚህ ይህንን
ቃል እና ተግባር ከጌታችን ከመዳሃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መማር ያገባናል፡፡ ትሁት መሆን ማለት ራስን ዝቅ ማድረግ ማለት ነው፡፡
ይህንንም ጌታችን መዳሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ሲመላለስ ሲያደርገው ኖሯል፡፡ አንድም ቀን ጌታ እራሱን ከፍ ያደረገበት
ጊዜ የለም፡፡ ከልደቱ እንኳን ብንጀምር በአህዬች እና በከብቶች ማደሪያ(በረት) ነው የተወለደው፡፡ እንደ ባለፀጋ እንደ ደሃ ልጅ
ሆኖ ነው ያደገው፤ የእንጨት ጠራቢ ልጅ፣ የድሃ ልጅ እየተባለ እየተሰደበ ነው ያደገው፤ ያለ ጫማ ያለመቀበሪያ ልብስ ነው ያደገው፤
በዚህም ምድር በኖረበት ጊዜ ያለማደሪያ ጎጆ ነው የኖረው፡፡ ሉቃ 9፤58 ቀን ቀን በቤተ መቅደስ ሲያስተምር ውሎ ለሊት ግን በደብረዘይት
ተራራ ሲፀልይ ያድር ነበር፡፡ ሉቃ 21፤37 መላእክት በሰማይ ከፍ
ከፍ የሚያደርጉት ጌታ በምድር ይህንን ሁሉ መፈፀሙ ለሰዎች አርአያና ቤዛ ለመሆን ነው በእለተ ሐሙስም የአስራ ሁለቱ ሐዋሪያትን
እግር ማጠቡ ሌላው ትህትናው ነው፡፡
የሚያሲዘውን የይሁዳ እግር እንኳን ሳይቀር ተጎንብሶ አጥቧል፡፡ ይህንን
ካደረገ በኃላ ግን ‹‹እናንተም እንዲህ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌን ሰጥቻችኃለሁ›› በማለት ለሐዋሪያት ተግባርን ጠቁሟቸዋል፡፡ ባጠቃላይ
ተናግሮ ተዘርዝሮ የማያልቅ የትህትናን ስራ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያከናውን ኖሯል፡፡ ይህንኑ ከእኔ ተማሩ በማለት
በአፅኖት ተናግሯል፡፡ ጌታችን ይህንን ሁሉ ምሳሌ ሰጥቶናል፡፡ ስለዚህ እርሱን ማየት ይገባናል፡፡ አብነት የሚሆን ባናገኝ እንኳን
አብነታችን እርሱ ነው፡፡ መምህራን ባይኖሩ እንኳን መምህራችን እርሱ ነው፡፡ ሰዎች የማይኖሩበት ብንኖር እንኳን ምሳሌያችን እርሱ
ነው፡፡ ይህንን ቃል ስንቅ በማድረግ ትህትናን የትም የት ልንፈፀመው እንችላልን ይልቁንም ማንኛውንም የመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ
ይህንን ትህትና ማጎልበት እንችላለን፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን ይህንን ቃል ባለሟቋረጥ ታስተምረናለች፡፡ ትህትና
ከምንም የሚቀድምና ከምንም የሚበልጥ የመንፈሳዊ አገልግሎቶች ሁሉ መነሻና መድረሻ ነው፡፡ ትህትና የሌለው ሰው ግን አገልግሎቱ ሁሉ
ግን ከንቱ ነው፡፡ ጌታ በሌላ የወንጌል ክፍል እንዲ በማለት አስተምሯል ‹‹እራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፤ እራሱን ግን
የሚያዋርድ ከፍ ይላል›› ሉቃ 18፤14 በዚህ ቃል መሰረት መጀመሪያ እራስን ዝቅ አድርጎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ከእመቤታችን
ከሐዋሪያትም ተምረናል፡፡ ሉቃ 1፤26 ጀምሮ ይመልከቱ፡፡ ለሐዋሪያት ጌታ እንዲህ ብሏቸዋል ‹‹በእናንተስ አይደለም ነገር ግን ማንም
ከእናንተ ታላቅ ሊሆን ቢወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፤ ከእናንተ ማንም ፊተኛ ሊሆን ቢወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን›› ማቴ 20፤26
በማለት ትልቁ መሳሪያ ትህትና እንደሆነ አስተምሯቸዋል፤ ሐዋሪያትም ያስተላለፉልን ይህንኑ ነውና ሁላችንም በአግልግሎት እራሳችንን
ዝቅ አድርገን ፤ ታዘን እሺ ብልን እንድናገለግል እንጂ ለስልጣን ፤ ለታይታና ለሙገሳ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ይህ ትምህርት
ከኢየሱስ ክርስቶስ ነውና በዚህም ቃል እንድንባረክ እንድንጠቀም እና ፍሬ እንድናፈራ የመንግስቱ ወራሾችም እንደንሆን የአምላካችን
ፍቃድ ይሁንልን፡፡ አሜን!!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፡- ፍሬ ሃይማኖት
/ጥር 2004ዓ.ም/ ልዩ እትም
No comments:
Post a Comment
ማህበረ ቅዱስ አሞኒ