Wednesday, February 29, 2012

ዐቢይ ጾም

/በ ተክለ-ሰማዕት/
     ዐቢይ ጾም ከጾሞች ሁሉ የሚበልት ትልቁ ጾም ሲሆን ጾሙ «ዐቢይ» የተባለውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ ከተጠመቀ በኋላ በገዳመ ቆሮንቶስ ለአርባ ቀናት የጾመው ጾም እና ታላላቅ የተባሉት ሦስት ኀጢአቶች ማለትም ስስት፣ ትዕቢትና ፍቅረ ነዋይ ድል የተነሡበት ጾም ስለሆነ ነው፡፡ ምሳሌው፣ አብነቱና አርአያነቱ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤የማቴዎስ ወንጌል «አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ጦሞ በኋላ ተራበ፡፡» (ማቴ 4፡2) ይላልና፡፡ በዚህ ጦሙም ሰይጣን ወደ እርሱ ቀርቦ በሦስት ዋና ዋና ኀጢአቶች (አርእስተ ኀጣውእ) ፈትኖታል፡፡ ገና ከመጀመሪያው ለምን ይጾም ዘንድ ወደ ገዳም ለመሔድ ወደደ? ለምንስ ጾመ? ለምንስ በሰይጣን ተፈተነ? ብለን ስንጠይቅ ዲያብሎስ በእርሱ ላይ የሚያረቀው በደልና ኀጢያት ኖሮበት ሳይሆን እኛን ተጠመቁ ሊለን እንደተጠመቀ እርሱ ጾሞ እኛን ጹሙ ሊለን ጾመ የሚል መልስ እናገኛለን፡፡ እኛ በምንጾምበት ጊዜ ሰይጣን እንድንበላ፣ ጌታን እንድንፈታተንና ለሀብትና ለንብረት እንድንበረከክ ሊያደርገን እንደሚመጣና ያን ጊዜም በእግዚአብሔር ቃል ድል ልናደርገው እንምንችል ሊያስተምረን ሲል እርሱ ጾመ፡፡ በተለይም ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ጭምር እንጂ በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር ሊገልጥልን ይህን አደረገ፡፡
     ዐቢይ ጾም የሚጾመው ለስምንት ሳምንታት ወይም ለአምሳ አምስት ቀናት ያህል ነው፡፡ ይህ እንዴት ይሆናል? ጌታ የጾመው አርባ ቀንና አርባ ሌሊት አይደለም ወይ? ብንል በእነዚህ 55 ቀናት ውስጥ   የሚገኙትን 7 ቅዳሜዎችና 8 እሑዶች ስንደምራቸው አሥራ አምስት ቀናት ይሆናሉ፡፡ በእነዚህ ቀናት ውስጥ ከጥሉላት እንከልከልባቸው እንጂ ከእህል ውኃ ስለማንከለከልባቸው እነዚህ 15 ቀናት ከዋናዎቹ የጾም ቀናት ገብተው አይቆጠሩም፡፡ ይህ ደግሞ ትክክለኛውን የጾም ቁጥር ወደ አርባ ዝቅ ያደርገዋል፡፡
በዐቢይ ጾም ውስጥ የሚገኙት 8 እሑዶች እያንዳንዳቸው የራሳቸው የሆነ ስያሜ አላቸው፡፡ እነርሱም ፡-
- 1ኛ ሳምንት ዘወረደ ይባላል ይህም አምላክ ከሰማይ መዉረዱን ሰዉ መሆኑንና ነገረ መስቀሉን ስለሚያወሳ ነዉ
-  2ኛ ሳምንት ቅድስት ይባላል ይህም ስለ ዕለተ ንበት ቅድስና ስለሚያወሳ ቅደስት ይባላል
-3ኛ ሳምንት ምኩራብ ይባላል ይህም ጌታ በመዋዕለ ትምህርቱ በምኩራብ ገብቶ ማስተማሩን የሚያወሳ ነው
- 4ኛ ሣምንት መፃጒዕ ይባላል ይህም ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድዉያንን መፈወሱና ዕዉራንን ማብራቱን የሚያነሳ መዝሙር ይዘመርበታል
-  5ኛ ሣምንት ደብረ ዘይት ይባላል ይህም በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሁኖ ጌታችን የዳግም ምጽአትን ትምህርት ያስተማረበት ስለሆነ ነው
-  6ኛ ሣምንት ገብርኄር ይባላል ይህም የጌታዉን ብር ያተረፈበት በጌታዉም ፊት ምስጋናን ያገኘበትን የተመሠገነበት ቀን ነዉ
- 7ኛ ሣምንት ኒቆዲሞስ ይባላል ይህም በለሊት ወደ ጌታ እየመጣ ይማር የነበረዉን የኒቆዲሞስን ታሪክ የሚያስታውስ ትምህርት በዚህ ሳምንት ይሰጥበታል
-  8ኛው ሳምንት ሆሳዕና ይባላል ይህም ጌታ በአህያ ዉርንጭላ ሆኖ ሆሣዕና በአርያም እየተባለ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት ዕለት መታሰቢያ ነዉ
-                በመጨረሻም ከሰርከ ሆሳዕና እስከ ትንሳኤ ያለዉ ሰባት ቀን ሕማማት ይባላል በዚህ ሳምንት ውስጥ በእያንዳንዱ ቀኖች ዉስጥ ብዙ አዝማደ መባልዕት አይበሉም፣ ስግደት ይሰገዳል፣ የጌታን መከራና ሞት የሚያስታዉሱ ምንባባት ከቅዱሳት መጻሕፍትና ከድርሳናት ተዉጣተዉ በግብረ ሕማማት ይነበባሉ እንዲሁም አዳም ከፈጣሪዉ ተጣልቶ የኖረዉን የጨለማ የመከራ ዘመን በማስታወስ መንበረ ታቦቱ በጥቁር ልብስ ይሸፈናል፡፡

     እግዚአብሔር አምላክ የጀመርነውን ጾም በሰላም በጤና ያስፈፅመን፡፡
የአምላካችን የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከእኛ ጋር ይሁን፤ አሜን!!!
                                  ወስብሐት ለእግዚአብሔር 

No comments:

Post a Comment

ማህበረ ቅዱስ አሞኒ