የብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የዓለም ሃይማኖቶች የሰላም የክብር ፕሬዝዳንት ሥርዓተ ቀብር ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት እንደሚፈጸም ዛሬ ጥዋት ቅዱስ ሲኖዶስ ተሰብስቦ ውሳኔ ካስተላለፈ በኋላ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶበታል፡፡
በማያያዝም የቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዓተ ቀብር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አባት ብቻ ሳይሆኑ የዓለም አብያተ ክርስቲያናትም አባት እንደመሆናቸው መጠን በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ሁሉም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምርያ ኃላፊዎችና መላ ሠራተኞች፣ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች በአጠቃላይ ሁሉም አገልጋዮች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን፣ መላ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ከውጭ የሚመጡ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአምስቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት ፓትርያርኮችና ልዑካኖች፣ የመንግስት ኃላፊዎችና አምባሳደሮች በተገኙበት እጅግ በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት እንደሚፈም አስረድቶአል፡፡
የሥርዓተ ቀብሩ መርሐ ግብርና አፈጻጸምም እንደሚከተለው ነው፡፡
ረቡዕ ነሐሴ 16 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀትር በኋላ የቅዱስ ፓትርያርኩ አስከሬን በሠረገላ ሆኖ በሚታይ መስተዋት ምዕመናን እያዩና ኃዘናቸውን እየገለጹ አዕይንተ እግዚአብሔር ካህናትም ስብሐተ እግዚአብሔር እያደረሱ ታጅቦ ወደ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይወሰዳል፡፡ እዛም እንደ ደረሰ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ ሥርዓተ ፍትሐት ይጀመራል፡፡ ሐሙስ ጠዋት ከሥርዓተ ቅዳሴ በኋላ የዓውደ ምሕረቱ መርሐ ግብር የሚፈጸም ሆኖ የቅዱስነታቸው የሕይወት ታሪክ በተፈቀደላቸው አባት ይነበባል፡፡ በመቀጠልም ቅዱሳን ፓትርያርኮች ኃዘናቸውን ይገልጻሉ፡፡ የመንግስት ባለሥልጣናትና አምባሳደሮችም በተመደበላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የኃዘን መግለጫቸውን ካነበቡ በኋላ የቀብሩ ሥርዓት ይፈጸማል፡፡
No comments:
Post a Comment
ማህበረ ቅዱስ አሞኒ