Saturday, August 18, 2012

በደብረ ታቦር ክብሩን አየን

     ደብረ ታቦር በግእዝ ቋንቋ ሲሆን የታቦር ተራራ ማለት ነው፡፡ (ማቴ 7÷1-8) የታቦር ተራራ የሚገኘው አሁን ፍልስጥኤም ተብሎ በሚጠራው ሀገር ነው፡፡ ደብረ ታቦር ወይንም የታቦር ተራራ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስት ደቀመዛሙርቱን ይዞ ወደ ተራራው የወጣበትና ፊቱ እንደፀሐይ የበራበት ልብሱም እንደብርሃን ነጭ የሆነበት ቦታ ነው፡፡ 
     ቤተ ክርስቲያናችን ከሚከበሩት ከዘጠኙ ዓበይት በዓላት አንዱ ደብረ ታቦር ነው፡፡ በዓሉ በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን 
በድምቀት ይከበራል፡፡ ታቦር ከገሊላ ባሕር በምእራባዊ ደቡብ በኩል 10ኪ.ሜ ርቆ የሚገኝ ተራራ ነው፡፡ ይህ ተራራ ከባሕር ጠለል 572 ሜትር ከፍታ አለው፡፡ «ባርቅ የተባለው ጦረኛ ሕዝበ እስራኤልን ይዞ በመዝመት ሲራ የተባለውን የሕዝብ ጠላት በታቦር ድል ነስቶ አሸንፏል» (መሳፍንት.4፡6-14)፡፡ 
     ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል፡፡ ክንድህ ከኃይል ጋር ነው ሲል በመዝሙር 88፡12 ስለ ታቦር ተራራ ዘምሯል፡፡ የታቦር ተራራ በገሊላ ከሚገኙ ተራራዎች አንደኛው ሲሆን በዛብሎን ክፍል ውስጥ ለሚኖሩ ልጆች የተሰጠ ቦታ ነው፡፡ 1ኛ ዜና.6፡77 ሐዲስ ኪዳን ግን ረጅም ተራራ ከማለት በስተቀር ታቦር ብሎ ስሙን አይጠራውም፡፡ ሆኖም ክርስቶስ በዚህ ተራራ ላይ ክብሩን እንደገለጠና የዚህም ተራራ ስም ታቦር መሆኑን ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው ገልጠዋል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም ይህንን ረጅም ተራራ ደብረ ታቦር እያለ በድጓው አስፋፍቶ ጽፏል፡፡ 
     ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ረጅም ተራራ የወጣው ብርሃነ መለኮቱን ክብሩን ለመግለጽ ነው፡፡ በዚህ ተራራ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙሴና ከኤልያስ ጋር ተነጋግሮአል፡፡ እነዚህም ሁለት ታላላቅ ሰዎች በበብሉይ ኪዳን ጊዜ ስለ ክርስቶስ ትንቢት የተናገሩ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ያስተማሩ ቅዱሳን ነቢያት ነበሩ፡፡
     ከነቢያት መካከል ሁለቱ ቅዱሳን ነቢያት እንዲገኙ ያደረገውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቂሣርያ ተገኝቶ «ደቀ መዛሙርቱን ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል) ሲል ጠየቃቸው ከእነሱም አንዳንዶቹ ኤልያስ፣ አንዳንዶቹም ሙሴ፣ ነው ይሉሃል አሉት፡፡ እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ) ቢላቸው አብዛኛዎቹ ኅብረተሰቡ ከሚለው ጋር ሲተባበሩ ቅዱስ ጴጥሮስ ግን አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ ሲል መሰከረ፤ ኢየሱስም መልሶ ይህን በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም አልገለጠልህምና ብፁእ ነህ አለው» (ማቴ.16፡13-18፡፡) 
    በዚህ አኳኋን ወደ ደብረ ታቦር ተራራ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ያዕቆብ ይዞ ወጥቶ ራሱ ኤልያስ ወይም ሙሴ አለመሆኑን ገለጠላቸው፡፡ ከሞተ ብዙ ዘመን የሆነውን ሙሴን ከመቃብር አስነስቶ ቀጥሎም በእሳት ሠረገላ ያረገውንና በተድላ ገነት የሚኖረውን ኤልያስን በተራራው እንዲገኝ አድርጐ አብረውት የነበሩት ደቀ መዛሙርት ሙሴ ነው ወይም ኤልያስ ነው በማለት ሲጠራጠሩ እንዳይኖሩ ትምህርት ለመስጠት ነው፡፡ 
     ማቴ.17፡2 «በፊታቸው ተለወጠ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ» ይላል፡፡ የክርስቶስ ፊቱ እንደ ፀሐይ የበራው የብርሃኑም ኃይል ያንፀባረቀው የብሉይ ኪዳን መሪ እንደነበረው እንደ ሙሴ ፊት ብርሃን አይደለም፡፡ «ሙሴ ከሲና ተራራ ሲወርድ የፊቱ ቆዳ አንፀባረቀ አሮንና እስራኤልም ይህንን ስላዩ ወደ እሱ ይቀርቡ ዘንድ ፈሩ ተሸፈንም እያሉ ጮኹ «ሙሴም እግዚአብሔር ያዘዘውን ለእነሱ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ በፊቱ መሸፈኛ አደረገ» ይላል፡፡ (ኦሪት ዘፀ.34፡29-30፡፡) የሙሴ የጸጋ ነው የክርስቶስ ግን የባሕርይ ነው፡፡ 
     «ብሩህ ደመና ጋረዳቸው» ይላል ይህ በሲና እንደታየው ያለ አይደለም፡፡ በታቦር የታየው ግን ብሩህ ነበር፡፡ በደብረ ሲና የተገለጠ የፍጡር የሙሴ ክብር ነበር፤ በደብረ ታቦር ግን የሕያው ባሕርይ የክርስቶስ ክብር ተገልጦአል፡፡

የደብረ ታቦር በዓል በቤተ ክርስቲያን በኩል ያለው አከባበር፡-
1ኛ. ደብረ ታቦር ከዘጠኙ አበይት በዓላተ እግዚእ አንዱ ነው፡-
     ከዋዜማው ጀምሮ እስከ በዓሉ ፍጻሜ ድረስ ማኅሌት ይቆማል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ስለ በዓሉ የደረሰው መዝሙር ይዘመራል፡፡ «ሰበሕኩከ በደብር በቅድመ ሙሴ ወኤልያስ ነቢያት ምእመናኒከ» በታማኞችህ ነቢያት በሙሴና በኤልያስ ፊት የባሕርይ ልጅነትህን መሰከርሁልህ የሚለው መዝሙር ለበሽሉ ልዩ ድምቀት ስጥቶት ይውላል፡፡

2ኛ. የደብረ ታቦር በዓል በቆሎ ተማሪዎች በኩል ያለው ይዞታ፡-
     የቆሎ ተማሪዎች በዓሉ አንድ ወር ሲቀረው በየመንደሩ ተዘዋውረው ጥሬ በልመና ይሰበስባሉ፤ ከለመኑትም ጥሬ ግማሹን ጠላ ይጠምቃሉ፣ ግማሹን ቆሎ ይቆሉታል፡፡ በዚህ ሁኔታ ሲዘጋጁ ይሰነብቱና በደብረ ታቦር እለት የለመኑትን ኅብረተሰብ የደብሩን ካህናትና አለቃ አስተማሪዎቻቸውን ጠርተው ይጋብዛሉ፡፡ በሚጋብዙበትም ወቅት እየዘመሩ ተጋባዡን ያስደስቱታል፡፡

3ኛ. የደብረ ታቦር በዓል ከኅብረተሰቡ ጋር ያለው የባህል ግንኙነት፡-
     ማንኛውም ኅብረተሰብ በዋዜማውና በየእለቱ ችቦ እያበራ ያከብረዋል፡፡ ሴቶችም በዋዜማው እንደ ጥብኝ ወይም ሙልሙል አድርገው ከስንዴ ዱቄት የተቦካ ዳቦ በብዛት ይጋግራሉ ወደ ቤት ሊጠይቅ ለሚመጣ ሰው ሁሉ ዳቦ ያቀርቡለታል፡፡ በጠቅላላው ዘመድ አዝማዱ ዳቦ እየተያዘ የሚጠያየቅበት የተነፋፈቀ ሁሉ የሚገናኝበት የተራራቀ ሁሉ የሚቀራረብበት በዓል በመሆኑ በዓሉ በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍ ያለ ተወዳጅነት አለው፡፡

4ኛ. የደብረ ታቦር በዓል በልጆች በኩል ያለው ሁኔታ፡-
     ወንዶች ልጆች ከዋዜማው ጀምሮ በቡድን፣ በቡድን የተከፋፈሉ ዳቦና ገንዘብ የሚቀበል ልጅ ከመካከላቸው ይመርጣሉ፡፡ ከዚያ በኋላ በየመንደሩ እየዞሩ የባህል ዘፈን እየዘፈኑና የሰጪዎችንም ስም እያወደሱ ዳቦና ገንዘብ ይቀበላሉ፡፡ በእለቱ እየጨፈሩ ካረፈዱ በኋላ ጨፍረው ያገኙትን ዳቦ አንድነት ተሰብስበው ይመገባሉ፡፡ ገንዘቡንም ተከፋፍለው ለየችግራቸው ያውሉታል፡፡

    የቡሄ ወይንም የደብረ ታቦር በዓል የተወደደና በጣም የሚናፈቅ ነው፡፡ የደብረ ታቦር በዓል በኅብረተሰቡና በልጆቹ በኩል የሚታወቀው ቡሄ በሚል ስም ነው፡፡ አባቶች ቡሄ ማለት በራ፣ ብርሃን ማለት ነው፡፡ በደብረ ታቦር የበራውን ብርሃን ያመለክተናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!

No comments:

Post a Comment

ማህበረ ቅዱስ አሞኒ