Monday, May 7, 2012

አንቲ ምሥራቅ ወወልድኪ ፀሐየ ጽድቅ፤


አንቺ ምሥራቅ ነሽ ልጅሽም እውነተኛ ፀሐይ ነው። /ድጓ/

ሊቀ ጠበብት ሐረገወይን አገዘ
     የቤተ ክርስቲያን አባት የእግዚአብሔር ወዳጅ ሆኖ ስለእመቤታችን ያልዘመረ ፣ያላመሰገነ ያልጻፈ የለም።ታላቁ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ የሚገባውን ንጽጽራዊ ምሳሌ ለሚገባት ወላዲት አምላክ ሰጥቶ አመስጥሮ ዘመረ። እንዲህ በማለት “ አንቺ የብርሃን መውጫ ምሥራቅ ነሽ፤ልጅሽም ከብርሃን የተገኘ ብርሃን እውነተኛ ፀሐይም ነው።”

       የቅዱስ ያሬድ ዝማሬያዊ ምስክርነት የተገለጠው ያለምክንያት አይደለም። የሰው ልጅ አታድርግ የተባለውን በማድረግና በፈጸመው ስህተት መውጫውም መግቢያም ጠፍቶበት ብርሃኑም የብርሃን፣ መውጫ በሩም ተሰውሮበት፣መንገዶቹ ሁሉ በጨለማ ሠራዊት ተዘግተውበት አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት ፍዳን ፣ዓመታተ ኩነኔን አሳልፏል። የሆነው ሆኖ የፈጣሪ ቸርነት ወሰን ገደብ የለውም በራሱ ምርጫ መኖሪያውን ጨለማ/ምድረ ፋይድ/ ውስጥ ያደረገውን የሰውን ልጅ ፤አንድ ቀን በምሥራቅ በኩል /እመቤታችን/ የሚወጣው እውነተኛ ፀሐይ /ኢየሱስ ክርስቶስ/ የበደል ጨለማውን እንደሚያስወግድለት የፈቃድ ቃልኪዳን ገባለት።ይህም በእውነት እንደሚፈጸም በነቢያቱ አንደበት አናገረ፣ አስተማረ፣ አጽናና። “ለእናንተ የጽድቅ ፀሐይ ትወጣላችኋለች። ፈውስም በክንፍቿ ውስጥ ይሆናል።” በማለት ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ የሚፈውስ ፣ የሚያድን ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ምሥራቅ ከተባለች ቅድስት ድንግል ማርያም እንደሚወለድ አስቀድሞ ተናገረ፤ ሚል. 4፥2 ።
 
    የእመቤታችንን የፅሐይ መውጫ ምሥራቅነት ቅዱሳን መጻሕፍት ተባብረውበታል።ነቢየ እግዚአብሔር ሕዝቅኤል አሟልቶ አጉልቶ ተናግሮታል። ሕዝ. 44፥1። በመሆኑም የፀሐይ መውጫ ምሥራቅ መሆኑ ከተረጋገጠ በቅድሚያ መገንዘብ ያለብን አስቀድሞ ስለተነገረው ምስጢር ነው።

     ምክኒያተ ድኅነት ወላዲተ አምላክ በብዙ ኅብረ አምሳል ተጠቅሳለችና ያን ሁሉ ለመዘርዘር ጊዜም ቦታም አይበቃንም ፤ ነገር ግን ምሥራቀ ፀሐይ ወላዲተ አምላክ በሌላ ነቢይ በሌላ ትንቢት ዝክረ ልደቷን በተመለከተ እንዲህ ተብሊ ተነግሯል።

     “ትውጽእ በትር እምስርወ እሴይ ፣ወየዐርግ ጽጌ እምኔሃ፤ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለች ከእርሷም አበባ ይወጣል።” ኢሳ 11፥1። እውነት ነው። ዛፍ ከሌለ አበባም ፍሬም የለም።መውጫ በር ከሌለ የሚገባ የሚወጣም የለም።አምላከ እግዚአብሔር ወልድ የጠፋውን ለመፈለግ፣ የወደቀውን ለማንሣት የሞተውን ለማዳን ምክንያት ያስፈለገው ነበር። ምክንያቱም የማዳን ሥራውን ለመሥራት መለኮታዊ ባሕርዩን ከሥጋዊ ባሕርይ ጋር ማዋሐድ ነበረበትና ነው።

      እግዚአብሔር ለአዳም በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለው የሚለውን የተስፋ ቃል በነቢያት አድሮ ማናገሩ የድኅነታችን መሠረት ያደረጋት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ነው። የሚከተሉት ሃይለ ቃላት የሚያረጋግጡት ይሔንን ነው።መዝ. 86፥1 መዝ 44፥ 10። የቸርነት ባለቤት አምላካችን የሰውን ልጅ ለመጎብኘት ጊዜው ሲደርስ ግንቦት አንድ ቀን ከማኅፀነ ሃና ምሥራቅ ፀሐይ ወላዲተ አምላክ ወጣች። ጎሕ ቀደደ የፀሐይ መውጫ አድማሱ ተገለጠ። ግሩም እለት በፈቃደአምላክ ፣ በብስራተ መልአክ ነሐሴ 7 ቀን የተፀነሰች ድንግል ማርያም በማኅፀን እያለችም የበረከት ሥራ የተአምራት ሥራ ትሠራ ነበር። ድውይ ፈውሳለች፤ ሙት አንስታለች፤ ለአምላክ እናትነት ለተመረጠች እመቤት ይህ ጉዳይ የሚበዛባት አይደለምና።

     ከእነዚህ ምክንያቶች የተነሣ የአይሁድ የምቀኝነት ሴራ በማየሉ የእመቤታችን ልደት የተፈጸመው በሊባኖስ ተራራ ላይ ነው። ለጊዜው ችግር ፈጣሪዎቹ የመልካም ነገር ጠላቶች አይሁድ ይሁኑ እንጂ የእርሷ በሊባኖስ ተራራ ላይ መወለድስ ትንቢተ ነቢያት ይፈጸም ዘንድ ነበር። መኅ. 4፥8 ። በመሆኑም ግንቦት አንድ ቀን በእመቤታችን ልደት የተገኘው በረከት ከድኅነተ ሥጋ ወነፍስ ጋር ተያይዞ ይነገር ለነበረው የትንቢተ ነቢያት አፈጻጸም የመጀመሪያው ብስራት ነበር።ምክንያቱም ስለጌታችን መወለድ የተነገሩ ትንቢቶች መነሻቸው እመቤታችን ከመሆኗም በላይ ስለራሷ ስለእመቤታችን የተነገሩትም ቢሆኑ ስፍር ቁጥር የላቸውም ።ዘፍ. 3፥15 ፤ኢሳ. 7፥14፤ መዝ. 44፥ 10። 

        ለዚህም ነው ቅዱስ ኤፍሬም አክሊለ ምክሕና ወቀዳሚተ መድኅኒት ወመሰረት ንጽሕነ ኮነ በማርያም ድንግል ፤ የመመኪያችን ዘውድ የደኅነታችን መጀመሪያ የንጽሕናችንም መሰረት … በድንግል ማርያም ተገኘልን እያለ ያመሠገናትም ለዚህ ነው። ዉዳሴ ዘሡሉስ ከዚህ በመነሣትም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ይህን ዐብይ የድኅነት መሠረት የሆነውን በዓል ቦታ ሰጥታ ታክበርዋልች። በዓሉ /ግንቦት 1/ ቀን በስሟበታነፁ አብያተ ክርስቲያናት ብቻ ሳይወሰን በሁሉም አብያተ ክርስቲያን በማኅሌት ፤ በሰዓታት ፤ በነግህ እና በሠርክ ጸሎት ነቅዳሴ በውዳሴ በዝማሬ ይከብራል። ምእመናንም ለእመቤታችን የተገባላትን ቃልኪዳን በማመን አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ መንፈሳዊውን እንደ መንፈሳዊነቱ፣ የቤተሰብን እንደ ቤተሰብ፣ የጐረቤትን እንደ ጐረቤት፣ ድሆችንም በአግባቡ በመመገብ በዓሉን መንፈሳዊ ዕሴቱን አስጠብቀው ያከብሩታል ያስከብሩታል።

      በተለይ የግንቦት ልደታ በዕለቱ ጐረቤቶች በአንድነት በመሆን ንፍሮ በመቀቀል ፣ ጠላ በመጥመቅ፣ ዳቦ በመድፋት፣ አብሮ በመብላት አብሮ በመጠጣት የበዓሉን ታሪካዊነት ያዘክሩታል። ምክንያቱም እመቤታችን የተወለደችው ከቤት ውጭ በተራራ ላይ ሲሆን ጐረቤት ዘመድ አዝማድ የቻለውን ያህል ይዞ ወደ ተራራው በመሔድ ቅድስት ሐናን የጠየቁበት አብረው የበሉበት የጠጡበት ዕለት ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያውን ያን በማስታወስ በዓሉን ታሪካዊ አድርገው ያከብሩታል። ይህ ዓይነት አከባበር የሚደገፍና መቀጠልም ያለበት መንፈሳዊ ዕሴት እንደሆነ ይታመናል።

መደረግ የሚገባቸው
     በዓሉ በመንፈስ ተጀምሮ በሥጋ እንዳይፈጸም ግን ሁሉም ምእመን ድርሻውን ሊወጣ ይገባዋል።ገላ 3፥3 ።በመሰረቱ አብሮ መብላት አብሮ መጠጣይት ያፋቅራል እንጂ አያጣላም፤ ያቀራርባል እንጂ አያራርቅም ። በዓሉን አብሮ እየተመገቡ ማክበር መልካም መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው። 

     ነገር ግን ለዚህ የበዓል አከባበር የሚዘጋጀውን ዝግጅት ከመሠረታዊ መታሰቢያነቱና ዓላማው ውጭ በተሳሳተ መንገድ አልፎ አልፎ አንዳንድ ግለሰቦች ወደ ባዕድ አምልኮ እየለወጡት ይታያል። በቤተ ክርስቲያናችን ትምህርትና ሥርዓት መሠረት ግንቦት አንድ ቀን የእመቤታችንን ልደት በማሰብ የሚከበር በዓል ሆኖ ሳለ ከግንቦት አንድ እስከ ሠላሳ ድረስ ድግስ በመደገስ፣ ንፍሮ እያነፈሩ ፣ ቆሎ እየቆሉ ፣ ያንንም ቅቤ እየቀቡ ፣ ኑግ እየወቀጡ፣ እያለጠለጡ ፣ ጠላ እየጠመቁ ፣ ዛፍ ሥር ወይም በየታዛው እየደፉ ይታያሉ።

      አነባበሮ በመጋገር ቅቤ በመቀባት ፣ አረቄ በመርጨት ፣ ዛፉንም በመቀባት አድባሯ ደስ እንዲላት በማለት ደም በማፍሰስ ወዘተ

     በዚህ ብቻ አያበቁም አይረኩም ቀይ በግ ቀይ ዶሮ ገብስማ ዶሮ ወዘተ በመምረጥ በማረድ በየመንገዱ ይጥላሉ ከዚህ ይልቅ ቢመገቡት በተፈወሱ ነበር። ሌላም አሳዛኝ ጉዳይ አለ። ለጠንቋይ የሐሰት ትምሕርት ልማዱ ነውና ከዚህ በመነሳት በግንቦት ወር መጋባት፣ እህል አውጥቶ መሸጥ ወዘተ አይገባም የሚሉም አልጠፉም። ይህ ወር አጋጣሚዬ /ገዴ/ አይደለም ከቤቴ አልወጣም የሚሉም አሉ። 

     ይህ ሁሉ መከራ የሚፈራረቁባቸው ወገኖች ያመኑ እየመሰላቸው ነገር ግን እምነታቸው ያልጸና ወገኖች ናቸው። የግንቦት ወር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደችበት ወር ፣ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢያሱስ ክርስቶስ ዕርገትና ርደተ መንፈስ ቅዱስ /ጰራቅሊጦስ/ የሚታሰብበት ወር ነው ግንቦት ከእነዚህ ታላላቅ በዓላት አኳያ የተቀደሰ ወር ነው። በዚህ ወር እንደ ቅዱስ ጋብቻ እና ሌሎችም የተቀደሱ ተግባራትን ማከናወን ይበልጥ መቀደስ ነው። በመሆኑም ወርኅ ግንቦትን ምክኒያት አድርገው ወደ ባዕድ አምልኮ የሚዋልሉ ሰዎች ከዚህ አስከፊ ድርጊት ተመልሰው ወደ አምላካቸው እንዲቀርቡ ያስፈልጋል። “ወደ እርሱ ቅረቡ እርሱም ያበራላችኋል” ተብሎ ተጽፏልና “ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አታምልክ ።” መባላችንንም አንርሳ ።

      የተቀደሰውን በዓል ስናከብር በቅድስና መሆን አለበት። “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” እንዳለ…1ኛ ጴጥ. 1፥16።

       የተከበረውን በዓል በሐይማኖት ስናከብር እኛም እንከብርበታለን። የበረቀት ተሳታፊዎችም እንሆናለን።

       ከዚህ ውጭ በሆነ ትምህርት እየተጓዝን በዓል እያከበርን ነው ብለን ስተን እንዳናስት ልንጠነቀቅ ይገባል። 


የአምላካችን ቸርነት የእናታችን አማላጅነት አይለየን። 


2 comments:

  1. u should express the source of ur article please!! U are doing it without understanding of copyright law!! I know this article on other media but u post it as ur work!! Great thiefing!!!

    ReplyDelete
  2. Dear our friend, first we thank you for the comment.
    we know this post is a cope from other site but we believe this post is very good for the readers.what we question is, what is the problem of posting this kind literature to spread for the readers?

    ReplyDelete

ማህበረ ቅዱስ አሞኒ