Thursday, August 23, 2012

ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ዓቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ሆነው መመረጣቸውን ቅዱስ ሲኖዶስ አስታወቀ


      የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሰኞ ዕለት ባደረገው ስብስባ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ዓቃቤ መንበር ሆነው መመረጣቸውን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል አስታወቁ፡፡ 

ብፁዕ አቡነ ናትኤል የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
     ብፁዕነታቸው ሰኞ ዕለት ከቀኑ 9፡30 ሰዓት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት ምልዓተ ጉባኤው  ሰኞ ባደረገው ስብሰባ ለቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዓተ ቀብር የሚመጡ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር እንግዶች በአግባቡ ማስተናገድ እንዲቻልና መንበርም ያለ ኃላፊ አንድም ቀን ማደር ስለማይገባ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 17 መሠረት በማድረግ ቀደምትነት ካላቸው ብፁዓን አባቶች መካከል ብፁዕ አቡነ ናትናኤል መመረጣቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ 

      ከዚህ በተያያዘ መልኩም ከዓቃቤ መንበር ብፁዕ አቡነ ናትናኤልና ከቋሚ ሲኖዶስ ጋር በመሆን ሥራውን የሚያከናውኑ ሥራ አስፈጻሚዎች ምልአተ ጉባኤው መሰየሙን ስማቸውን ጠቅሶ አስረድተዋል፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተሰየሙ ብፁዓን አባቶች ስም ዝርዝር እንደሚከተለው ነው፡፡ 

Wednesday, August 22, 2012

የብፁዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት የዓለም የሰላም አምባሳደር የቀብር ሥነ ሥርዓት የወጣ መርሐ ግብር

"ለፈራሔ እግዚአብሔር ይሤኒ ደኅሪቱ፣ ወይትባረክ ዕለተ ሞቱ"
"እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ፍፃሜው ያምራል፡፡ በሚሞትበትም ቀን ይከበራል" ሲራ. 113፡፡
     የብፁዕ ወቅዱስ / አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት የዓለም የሰላም አምባሳደር የቀብር ሥነ ሥርዓት የወጣ መርሐ ግብር

/           
       
          ሰዓት

                                                    ክንውን
1
ጠዋት 1200 
 ረቡዕ ነሐሴ 16 ቀን 2004 . በኢትዮጵያ ገዳማትና አድባራት 10 ደቂቃ ያህል የደወል ድምጽ ይሰማል፡፡                   
2
ከቀኑ 500 - 530
በዚሁ ዕለት ከቀኑ 500 ሰዓት የቅዱስነታቸው አስከሬን በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣
የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ኃላፊዎችና መላው ሠራተኞች፣ የየድርጅቱና የየኮሌጁ ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ 
የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራ አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎች፣ ሠራተኞች፣ መላ አገልጋዮች በክብር ታጅቦ ከመንበረ ፓትርያርክ 
ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ቤተ ክርስቲያን ይገባል፡፡
3
ከቀኑ 530 – 830
 የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ይከናወናል፡፡
4
ከቀኑ 830 – 1200

Saturday, August 18, 2012

በደብረ ታቦር ክብሩን አየን

     ደብረ ታቦር በግእዝ ቋንቋ ሲሆን የታቦር ተራራ ማለት ነው፡፡ (ማቴ 7÷1-8) የታቦር ተራራ የሚገኘው አሁን ፍልስጥኤም ተብሎ በሚጠራው ሀገር ነው፡፡ ደብረ ታቦር ወይንም የታቦር ተራራ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስት ደቀመዛሙርቱን ይዞ ወደ ተራራው የወጣበትና ፊቱ እንደፀሐይ የበራበት ልብሱም እንደብርሃን ነጭ የሆነበት ቦታ ነው፡፡ 
     ቤተ ክርስቲያናችን ከሚከበሩት ከዘጠኙ ዓበይት በዓላት አንዱ ደብረ ታቦር ነው፡፡ በዓሉ በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን 
በድምቀት ይከበራል፡፡ ታቦር ከገሊላ ባሕር በምእራባዊ ደቡብ በኩል 10ኪ.ሜ ርቆ የሚገኝ ተራራ ነው፡፡ ይህ ተራራ ከባሕር ጠለል 572 ሜትር ከፍታ አለው፡፡ «ባርቅ የተባለው ጦረኛ ሕዝበ እስራኤልን ይዞ በመዝመት ሲራ የተባለውን የሕዝብ ጠላት በታቦር ድል ነስቶ አሸንፏል» (መሳፍንት.4፡6-14)፡፡ 
     ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል፡፡ ክንድህ ከኃይል ጋር ነው ሲል በመዝሙር 88፡12 ስለ ታቦር ተራራ ዘምሯል፡፡ የታቦር ተራራ በገሊላ ከሚገኙ ተራራዎች አንደኛው ሲሆን በዛብሎን ክፍል ውስጥ ለሚኖሩ ልጆች የተሰጠ ቦታ ነው፡፡ 1ኛ ዜና.6፡77 ሐዲስ ኪዳን ግን ረጅም ተራራ ከማለት በስተቀር ታቦር ብሎ ስሙን አይጠራውም፡፡ ሆኖም ክርስቶስ በዚህ ተራራ ላይ ክብሩን እንደገለጠና የዚህም ተራራ ስም ታቦር መሆኑን ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው ገልጠዋል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም ይህንን ረጅም ተራራ ደብረ ታቦር እያለ በድጓው አስፋፍቶ ጽፏል፡፡ 
     ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ረጅም ተራራ የወጣው ብርሃነ መለኮቱን ክብሩን ለመግለጽ ነው፡፡ በዚህ ተራራ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙሴና ከኤልያስ ጋር ተነጋግሮአል፡፡ እነዚህም ሁለት ታላላቅ ሰዎች በበብሉይ ኪዳን ጊዜ ስለ ክርስቶስ ትንቢት የተናገሩ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ያስተማሩ ቅዱሳን ነቢያት ነበሩ፡፡

የቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዓተ ቀብር ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም እንደሚፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ አስታወቀ፡፡




      የብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የዓለም ሃይማኖቶች የሰላም የክብር ፕሬዝዳንት ሥርዓተ ቀብር ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት እንደሚፈጸም ዛሬ ጥዋት ቅዱስ ሲኖዶስ ተሰብስቦ ውሳኔ ካስተላለፈ በኋላ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶበታል፡፡ 

Thursday, August 16, 2012

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ አረፉ


ብፁዕነታቸው ያለፈው እሁድ በቅዳሴ ላይ እንደነበሩ ከውስጥ አዋቂዎች ለመረዳት የቻልን ሲሆን  ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በጠና ታመው ነሐሴ 8/2004ዓ.ም ማምሻውን ወደ ደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ለህክምና ገብተው በዶክተሮች ክትትል ሲደረግላቸው ቆይተው ትላንት ለሊት ሊያርፉ ችለዋል፡፡  
የአባታችንን ነፍስ በገነት ያኑርልን አሜን፡፡

Friday, August 10, 2012

ፍልሰታ ለማርያም

እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ፡፡ 
          ፍልሰታ ማለት ፈለሰ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር የነበሩበትን ሀገር ለቆ ወደ ሌላ ሀገር መሰደድ መፍለስ ማለት ነው፡፡ ጾመ ፍልሰታ ሲባልም የእመቤታችን ሥጋ ከጌቴሰማኒ ወደ ገነት መፍለስን በኋላም በገነት በእፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገርነው፡፡ 
       እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም 64 ዓመት በዚህ ዓለም ኖራ በሞት ከተለየች በኋላ እንደ አንድ ልጅዋ ሞታ መነሣቷንና እርገቷን ያዩ ዘንድ ሐዋርያት ከነሐሴ 1 እስከ 16 የጾሙት ጾም ነው፡፡ ጾመ ፍልሰታ ከሰባቱ አበይት አጽዋማት አንዱ ሆኖ በቀኖና እንዲጾም ከተወሰነበት ጊዜ ጀምሮ ምእመናን ይጾሙታል፡፡
          እመቤታችን በ5485 ዓ.ዓ ከአባቷ ከኢያቄም ከእናቷ ከሐና “እም ሊባኖስ ትወጽእ መርዓት፡፡ ከሊባኖስ ሙሽራ ትወጣለች” ተብሎ በተነገረው መሠረት ነሐሴ 7 ቀን ተጸነሰች፡፡ ግንቦት አንድ ቀን ሊባኖስ በምትባል ወረዳ በብጽአት እንደተወለደች የቤተክርስቲያን ታሪክ በሰፊው ያስረዳል፡፡ በጾም በጸሎት በአስተብቁኦት የተገኘች ናት፡፡ ንጽሕት በመሆኗም ማኅደረ እግዚአብሔር ሆናለች፡፡