Monday, June 18, 2012

የሰኔ ቅዱስ ሚካኤል ድርሳን

በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በማመን በባሕርይ በህልውና አንድ አምላክ ብለን አምነን ሰኔ በባተ በዓሥራ ሁለት ቀን የመላእክት ሁሉ አለቃ የሚሆን የቅዱስ ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ እንዲከበር እንናገራለን ልመናው አማላጅነቱ ከሁላችን ጋር ይኑር ለዘለዓለሙ አሜን።
እግዚአብሔርን እጅግ አድርጐ የሚፈራ ወር በገባ በየዐሥራ ሁለቱ ቀን የቅዱስ ሚካኤልን ዝክሩን የሚዘክርና ይልቁንም በኅዳር ዓሥራ ሁለትና በሰኔ ዓሥራ ሁለት ቀን በታላቅ ክብር የሚያከብር አንድ ሰው ነበር።
ለዚህ እግዚአብሔርን ለሚፈራ ሰውም ርኅራኄ የሌለው በሱም ላይ ጥላቻ ያደረበት በለጸጋ ጐረቤት ነበረው የቅዱስ ሚካኤልን በዓል በሚያከብርበት ጊዜ ሁሉ ይዘብትበት ይሳለቅበት ነበር።
ይህ እግዚአብሔርን ለሚፈራ ሰውዬ በዚህ ዓይነት በጐ ሥራ ብዙ ጊዜ ከኖረ በኋላ ከዚህ ዓለም ድካም ያርፍ ዘንድ የሞቱ ጊዜ ቀረበ።