Sunday, March 18, 2012

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሲኖዳ 3ኛ አረፉ


 ግብፅ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትና የቅዱስ ማርቆስ መንበር 117ኛ ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሲኖዳ 3ኛ መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ.ም በ 88 ዓመታቸው በካንሰር ሕመም ምክንያት ከዚህ ዓለም ድካም ዐርፈዋል፡፡
በሰሜናዊ ግብፅ፣ አስዩት ውስጥ ሐምሌ 27 ቀን 1915 . ሲወለዱ ናዚር ጋይድ የሚል መጠሪያ ከቤተሰባቸው የተሰጣቸው ቅዱስነታቸው፣  ቅስናን ሲቀበሉ አባ እንጦንስ ተብለው ይጠሩ የነበር ሲሆን አቡነ ሲኖዳ የተባሉት 1955 . የክርስትና ትምህርት ኤጲስ ቆጶስ ተብለው በተሾሙበት ወቅት ነበር፡፡ ቅዱስነታቸው አቡነ ሲኖዳ የቅብጥ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን 117 ፓትርያርክ ሆነው በወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ መንበር ላይ የተሾሙት ከተአምር ሠሪው ፓትርያርክ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ 6 በኋላ ኅዳር 4 ቀን 1964 . ነበር፡፡

ቅዱስነታቸው በአገልግሎት ዘመናቸው ከ 3 የአሜሪካ እንዲሁም ከ 1 የጀርመን ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት የተቀበሉ ሲሆን ባለፉት 20 ዓመታት የዓለምን ሕዝብ ያስተማሩባቸው የ80 መጻሕፍት ደራሲና የቤተ ክርስቲያኗ ኦፊሴላዊ መጽሔት ኤል-ኬራዝ ዋና አዘጋጅ ነበሩ፡፡
 በግብፅ ርዕሰ ብሔር አንዋር ሳዳት ጊዜ አክራሪ ሙስሊሞች በክርስቲያኖች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት መጨመርና መፋፋም ያሳሰባቸው ቅዱስነታቸው በመንግሥቱ ላይ ባነሱት ተቃውሞ፣ 40 ወራት ከመንጋዎቻቸው ተለይተው ወደ ቅዱስ ቢሶይ ገዳም ተግዘው የአባቶቻቸውን በረከት ተካፍለው እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን በኋለኛው መሪ ሆስኒ ሙባረክ ዘመን ወደ መንበራቸው ተመለሰው እስከ ዛሬ ድረስ ጠቦቶችን ሲጠብቁ፣ ግልገሎችና በጎችን ሲያሰማሩ ቆይተው ዐርፈዋል፡፡



በግብፅ ሕዝብ በተለይም በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ተወዳጅ አባት እንደሆኑ የሚነገርላቸው ቅዱስነታቸው በግብፃውያን ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻልና ሰላማዊ ለማድርግ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እንደደከሙ ይመሠከርላቸዋል፡፡



ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሲኖዳ ኢትዮጵያን  ሁለት ጊዜ የጎበኙ ሲሆን ከመጀመሪያው ጉብኝታቸው 30 ዓመታት በኋላ 2000 . ሚያዝያ ወር ላይ ያደረጉት ጉበኝት የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነበር፡፡



ጸሎታቸው ከሁላችን ጋር ይሁን፣ ማኅበራችን ማኅበረ ቅዱስ አሞኒ ለግብፃዉያን ወንድም እህቶቻችንና ቅዱስነታቸውን ለሚወዱ ሁሉ መጽናናትን ይመኛል፡፡

No comments:

Post a Comment

ማህበረ ቅዱስ አሞኒ